በተለያየ ምክኒያት በኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ ዑለሞች፣የቲም አሳዳጊዎች እና እስልምናን የተቀበሉ የማህበረሰባችን ክፍሎች ከኢኮኖሚ ጫና እንዲላቀቁ የስራ እድል በመፍጠር፣ዘላቂ ድጋፎችን በማመቻቸትና ሁለ-ገብ ማዕከላትን ማስተዳደር አስፈላጊ ነውና በዚህ አላማ ዘርፉን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ይህ ዘርፍ በርካታ ተግባራትን በማከናዎን ላይ የሚገኝ ሲሆን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በዳሰሳ ጥናት በመታገዝ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።በዋናነት ከሚጠቀሱ ተግባራት መካከል በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚታየዉን የአክፍሮተ ሃይላት ዘመቻን ለመግታት ብሎ ምሰዎች የኢስላምን ብርሃን እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ያለዉ ስራ ተጠቃሽ ነዉ።እንደሚታወቀዉ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩባቸዉ አካባቢዎች የሚሽነሪ እንቅስቃሴ ጎልቶ መታየት መጀመሩን ተከትሎ የኢኮኖሚ ጥገኝነታቸዉን በመጠቀም ከእለት ጉርስ በማታልፍ ጥቅም እምነታቸዉን ጥለዉ የሌላ እምነት ተከታይ እንዲሆኑ እየተገደዱ ይገኛሉ።

ይህ የሚያሳየዉ የሌሎችን ጥንካሬ ሳይሆን የእኛን ድክመት ነዉና በፍጥነት ሊገታ ይገባል ከሚል እምነት በመነሳት ኢማን ኢስላማዊ ማህበር ከነዚህ አካባቢዎች መስጅዶችን በማስገንባት መድረሳዎችን በማቋቋምና ዳዒወችን በማሰማራት መሰረታዊ እምነታቸዉን የሚያዉቁበትን ስርአት መዘርጋት ችላለች።

በተለያዩ አቅጣጫዎች በሙስሊሙ ወገኖቻችን ላይ ያንዣበበዉ አደጋ እንዲህ ያለ መልክ አለዉ።ይህንን ሰፊ ችግር ለመጋፈጥ ኢማን ኢስላማዊ ማህበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች ከነዚህም መካከል በከረዩ የተሰራው ለአብነት ይጠቀሳል ሰዎች ዲናቸውን እንዲገነዘቡ በራሳቸው ቋንቋ የሆኑ ወደ 997 የሚሆኑ ኢስላማዊ መሰረታዊ መፅሀፍቶች ተበርክተዋል። አሁንም በመደረግ ላይ ይገኛል።ከዚህም በተጨማሪ ለአይነ ስዉራን የብሬል ቁርአን አበርክታለች።

ሌላኛዉና ልዩ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ ለገጠር አሊሞች የኪታብ ድጋፍ በማድረግ መሆኑን የተረዳችዉ ኢማን ይህንን ጉዳይ እንደዋና ተግባሯ በማየት በመስቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።እንደሚታዎቀዉ የገጠር አሊሞች ምንም እንኳ በእዉቀት የበለፀጉ ቢሆኑም ተማሪዎቻቸዉን የሚያስተምሩበት ኪታብ በማጣት ለዘመናት ሲንከራተቱ ቆይተዋል።በተለይም የማጣቀሻ ኪታቦች እጥረት በርካታ ተማሪዎቻቸዉን እየበተነባቸዉ የሚያስተምሩበት ማእከል እስከ መዘጋት የደረሰበት ወቅት መከሰቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነዉ።

የነዚህ የማጣቀሻ ኪታቦች ዋጋ ከፍተኛ መሆኑንና እንደ ልብ አለመገኘት እዉቀታቸዉን በተገቢዉ መልኩ እንዳያስተላልፉ እክል ሆኖባቸዉ እንደቆየ የሚገልፁት እነዚሁ አሊሞች የሚደረግላቸዉ ጥቂት ድጋፍ ስሜታቸዉን ሲያድሰዉ ማስተዋል ከባድ አይሆንም።

በተጨማሪም የገጠር መሻኢኾች በገጠማቸዉ ኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት ወደ ከተማ መፍለስና ከፍሲልም ባህር አቋርጦ መሰደድ እየፈጠረ ያለዉ ችግር የዒልምን ማእከላት ከማራቆትም አልፎ ተተኪ አሊሞችን የማገኘት ተስፋን እያጨለመ ይገኛል።ለዚህም ኢማን እነዚህ ብርቅ የአሊሞች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ቀያቸዉን ለቀዉ እንዳይፈልሱና እንዳይሰደዱ ባሉበት ሆነዉ ስፖንሰር የሚደረጉበት ሁኔታ እያመቻቸች ትገኛለች። በተጨማሪም 9000 ቁርአኖችንና 12000 የተለያዩ ኪታቦችን በገጠር ለሚገኙ መሻኢኾችና ደረሳዎች አከፋፍላለች። ኢማን በዚህ ብቻ ሳትወሰን ለ20 ዓሊሞችና ዳዒዎች በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ እየሰጠች ትገኛለች።

ኢማን ኢስላማዊ ማህበር በረመዷንና በዒዶች ወቅት ማፍጠሪያና ተደስቶ መዋያ አቅም ለሌላቸዉ ወገኖች የደስታቸዉን እለት በሃዘን እንዳያሳልፉት ለ 22000 ሰዎች የረመዷን ኢፍጧር እናለ 39070 ሰዎች ኡዱሁያ በማከፋፈል አለሁላችሁ እያለች ትገኛለች።በተለይ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ችግሩ ገዝፎ የሚታይ በመሆኑ ዛሬ ነገ ሳይባል አቅም በቻለ ሁሉ ለነዚህ ወገኖች ሊደረስላቸዉ ይገባልና ኢማን ይህንን በማስመልከት የተለያዩ የባእላት ቀናትና የረመዷን ቀን የኢፍጧርና ኡዱሁያ ፕሮግራሞችን አዘጋጅታለች።እንዲሁም ባእላትን በማስመልከት ለ 2000 ሰዎች የሙሉ ልብስ ስጦታ አከናዉናለች።ይህ ተግባር በዘላቂነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉንም ርብርብ የሚሻ ጉዳይ ነዉና ቸል ሊባል አይገባም።

ኢማን ኢስላማዊ ማህበር የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በመንደፍ ቅርንጫፎቿን በማስፋት ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ተግባራትን በማከናዎን ረጅሙን መንገድ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን እየተጓዘች ትገኛለች።

በቀጣይም አድማሷን በማስፋት ኢስላማዊ ዩኒቨርስቲ እና ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ ማህበራዊ ተቋማትን በአጋሮቿ ድጋፍና እገዛ ለማቋቋም ኑ እንዲህላለዉ የተቀደሰ ተግባር እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንጓዝ ስትል ጥሪዋን ታስተጋባለች።

በዚህ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን በጥቂቱ

የቁርዓን ሂፍዝ ማዕከላት ማደራጀት

•     በደቡብ ክልል

•     በኦሮሚያ ክልል

•     በአማራ ክልል

•     እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዳዲስ የቁርዓን ሂፍዝ ማዕከላትን በመክፈት ለዲኑ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከ700 በላይ የቁርዓን ሂፍዝ ተማሪዎችን ለማስመረቅ ችሏል! በ100ዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችንም በማስተማር ላይ ይገኛል!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here